መጋቢት 26 ፣ 2018 _ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተቀረጸው አገራዊ የጤና ፖሊሲ፤ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑ ተገለፀ።
ኤፍ ቢ (FB) የተሰኘ የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ያመረታቸውና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠሙ ባለሦስት እግር አምቡላንሶችን በሀረማያ ዩንቨርስቲ ሕይወት ፋና ሁሉን አቀፍ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ሚኒስቴር ልኡካን በተገኙበት የሥራ ጉብኝት ተደርጎባቸዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ድኤታ አማካሪ ፕሮፌሰር ስለሺ ጋሮማ እንደገለጹት በጤናው ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ለአገልግሎቱ መሳለጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
መንግሥት የሕክምና መሣሪያዎች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፤ እነዚህ ባለሦስት እግር አምቡላንሶች የእናቶችንና የሕፃናትን ሕይወት ለመታደግ እንዲሁም የድንገተኛ ሕክምናን ተደራሽ ለማድረግ የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በተለያዩ ደረጃ በጤና አገልግሎቶች ስራ ላይ እንዲውሉ የሚሰራና አገለግሎቱን የሚያበረታቱ መሆኑን ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር የሕክምና አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ኢሊባቦር ቡኖ በበኩላቸው ለእይታ የቀረቡት አምቡላንሶቹ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
የሆስፒታሉ የላይዘን አገልግሎት ክፍል ኃላፊ አቶ አሰፋ ዘለቀ በኤሌክትሪክ የሚሠሩት እነዚህ አምቡላንሶች የነዳጅ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንሱና አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኤፍ ቢ (FB) የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ተወካይ ወይዘሮ ነኢማ አብደላ በበኩላቸው አምቡላንሶቹ በተለይ በትላልቅ ተሽከርካሪዎች ለመድረስ አዳጋች በሆኑ መንደሮች ውስጥ ዘልቀው በመግባት ሕይወት ለመታደግ የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንዲህ ያሉ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ መገጣጠም የውጭ ምንዛሬ ጫናን ከመቀነስ ባለፈ፣ የጥገናና አቅርቦትን በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች የተሟሉላቸው እና የሀገር ውስጥ የፈጠራ ውጤቶች የሆኑት አምቡላንሶች ለጤና አገልግሎቱ መዘመንና ለሕዝቡ እፎይታን ለመስጠት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።




